image
image
image
image
image

የውጭ ምንዛሬን በማስቀረትና የሀገር ኢኮኖሚ በማረጋጋት ረገድ በመስሪያ ቦታዎች የሚመረቱ ተኪ ምርቶች ሚና ከፍተኛ ነው ተባለ።

ሰኔ 9, 2018
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የመስሪያ ቦታዎች ልማት ጽህፈት ቤት የምክር ቤት አባላት የመማክርት ጉባኤ፣ የሲቪክ ማህበራት እና የመስሪያ ቦታዎች የግቢ ኮሚቴ በጋራ በመሆን በክፍለ ከተማው በሚገኙ የማምረቻ ሼዶች ላይ የመስክ ምልከታ አደርገዋል። በጉብኝቱ በሼዶች ውስጥ የተሰማሩ አንቀሳቃሾች የሀገር ውስጥ ምርትን በመተካት ገበያን በማረጋጋት እና ሰፊ የስራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ያላቸውን ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል። የመስሪያ ቦታዎች ልማት ፅ/ቤት ያስገነባቸውና እያስገነባቸው ያሉ የመስሪያ ቦታዎች ለአምራቾች ምቹ ሁኔታን የፈጠሩና ምርታማነትን በመጨመር በአገር ኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ያላቸው መሆኑ ከመስክ ምልከታው መረዳት ተችሏል። ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተሟላላቸውና ጽዳታቸው የጠበቁ እነዚህ የመስሪያ ቦታዎች በተቋሙ በሚደረግላቸው ተከታታይ ድጋፍ የካይዘን አተገባበር መሠረት አድርገው የሚሰሩ መሆናቸው ውብና ለስራ ምቹ እንዲሆኑ እንደሰዳቸውም መመልከት ተችሏል። የመስክ ምልከታው የአምራቾችን አቅም በመገምገም በሼዶች ውስጥ ያሉ ማህበራትና ኢንተርፕራይዞች ያሉባቸውን የስራ እንቅስቃሴና የስራ ቦታ አጠቃቀም በመመልከት ችግሮችን ለመፍታት በመስሪያ ቦታዎች በኩል ያሉ የመሰረተ ልማትና የአሰራር ክፍተቶችን ለይቶ ድጋፍ እና ክትትል ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ተቋሙ ገልጿል። በባለ ድርሻ አካላትና በአምራቾች መካከል ቀጥተኛ የሃሳብ ልውውጥ በማድረግ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት እንደዚህ አይነት የመስክ ጉብኝቶች ሚና የላቀ እንደሆነም ተሳታፊ ባለ ድርሻ አካላትና አምራቾች ሀሳብ ሰጥተዋል። ተኪ ምርቶችን በማምረት ረገድ የተመዘገቡ ስኬቶች በጉብኝቱ ወቅት የተብራሩ ሲሆን በበርካታ ኢንተርፕራይዞች ከዚህ ቀደም ከውጭ ሀገር በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት እንደተቻለም ተገልጿል። የውጭ ምንዛሬን ከማዳን አኳያም በአልባሳት፣ በቆዳ ውጤቶች፣ በጽዳት መጠበቂያ ግብዓቶችና በምግብ ማቀነባበር ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾች የገቢ ምርቶችን በከፍተኛ ደረጃ እየተኩ እንደሆነ መገንዘባቸው የጉብኝቱ ተሳታፊዎች አስረድተዋል። በሌላ መልኩ የገበያ ዋጋን በማረጋጋት ምርቶችን በቀጥታ ከአምራች ወደ ሸማች እንዲደርስ በማድረግ የኑሮ ውድነቱንና የገበያ መናጋቱን ለመቀነስ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሆነም ነው የተገለጸው። የሀገር ውስጥ ምርቶች ከውጭ ከሚገቡት እኩል ተወዳዳሪ በመሆን በተለያዩ ተቋማት ስራ ላይ ውለው በተግባር ታይቷል ያሉት አምራቾቹ የጥራት የመለዋወጫ እና የባለሙያ ግብዓት በራስ አቅም በሚሸፈን መንግስት በዘረፉ የያዘውን አላማ በማሳካት ላይ መሆናቸውን አስረድቷል። ይህ በክፍለ ከተማው የተዘረጋው የመስሪያ ቦታዎች ልማት ለአካባቢው ወጣቶችና ሴቶች አዲስ ተስፋ የፈነጠቀ መሆኑ በጉብኝቱ ወቅት ለማስተዋል ተችሏል። በሼዶቹ አማካኝነት በሺዎች ለሚቆጠሩ ስራ አጥ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር የቴክኖሎጂና ክህሎት ሽግግር በማድረግ ወጣቶች በተግባር የታገዘ የስራ ላይ ስልጠና አግኝተው ራሳቸውን እንዲችሉ አግዟልም ተብሏል። ኢንተርፕራይዞች ከማሸጋገር አንጻር እንደ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ ስድስት ኢንተርፕራይዞች ከጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ(ዶክተር) በገላን ጉራ የኢንዱስትሪ መንደር 1ሺ 300 ካሬ በመረከብ ወደ አምራች ኢንዱስትሪነት ማደጋቸውም ከጉብኝቱ ገለጻ ማወቅ ተችሏል። በጉብኝቱ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ከአምራቾች ለተነሱላቸው የገበያ ትስስርና ሌሎች ክፍተቶች ለመፍታት ከሚመለከታቸው የከተማው አስተዳደር አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል። የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የመስሪያ ቦታዎች ልማት ጽህፈት ቤት ያመቻቻቸው እነዚህ ሼዶች የሀገርን ምርታማነት በማሳደግና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድ ያላቸው ሚና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ማለቱና ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ከወትሮው በተሻለ በመስራት ላይ እንደሚገኝ መግለጹን የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት የዜና ክፍል ዘግቧል።

መልዕክትዎን ይላኩ

ሌሎች ዜናዎች